በዶ/ር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሠራተኞች የተቋቋመው Humanitarian and social service unit (HASSU) የተሰኘ የበጎ አድራጎት ማህበር ለ155 አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የመማሪያና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የዶ/ር ቦጋለች ገብሬ መ/ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ደረበ ዮሐንስ ድጋፉ የማህበሩ አባላት ከደመወዛቸው በየወሩ ለዚሁ መልካም ተግባር ብሎ በሚያዋጡት መዋጮ እና በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ቅን ልቦች ያላቸውን ወገኖች በማስተባበር በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የደሃ ደሃ ለሆኑ ቤተሰብ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ ታስቦ የተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። በተለያዩ የኢኮኖሚ ችግሮች ምክኒያት ተረጂ ለሆኑ ልጆች ድጋፉ እንዲደረግ የድርሻቸውን ለተወጡ ለሆስፒታሉ ሠራተኞች፣በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ለሚገኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ዶ/ር ደረበ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በዶ/ር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የHumanitarian and social service unit/HASSU/ አስተባባሪ አቶ አዲስዓለም ደጃሾ ማህበሩ በሰብዓዊና ማህበራዊ ጉዳዮች የሚያገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት አላማ ሰንቆ የተቋቋማ መሆኑን በመግለፅ በጤና፣ በትምህርት፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን አቅም በፈቀደው ሁሉ የድጋፍ እጆቹን ይዘረጋል ነው ያሉት። ማህበሩ ለ155 አቅም ለሌላቸው ቤተሰብ ልጆች የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስና ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ማድረጉን ነው የገለፁት።